በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አስተዳደር ዓመታዊ የመምህራንና የተማሪዎች ስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ጀመረ።
=======================
መጋቢት 5/2015 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ)
“የመምህራን ህብረት ለከተማችን ሰላምና ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽ/ቤትና ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የመምህራንና የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ዛሬ ጀምሯል።
ፌስቲቫሉ ከመጋቢት 5-15/2015 ዓ.ም ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የእግር ኳስ፤ መረብ ኳስ፤ ጠረጴዛ ቴኒስ፤ ዳርትና ቼዝን ያካተተ እንደሆነ በወጣው የውድድር መርሀ ግብር ተመላክቷል።
በውድድሩ የሁሉም ወረዳ ከ450 በላይ መምህራን መካከልና በ2ኛ ደረጃ እንዲሁም 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል የሚካሄድ መሆኑን በቃሊቲ ት/ቤት በተካሄደው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ተገልጿል።
የፌስቲቫሉ ዓላማ በመምህራን መካከልና በተማሪዎች መካከል ውድድር በማካሄድ ወንድማማችነትና መቀራረብን ብሎም የአንድነት መንፈስን ለማስረጽ እንዲሁም በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመፍጠር አንደሆነ ተጠቅሷል።
በመክፈቻ መርሀ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ (ተወካይ) አቶ ከበደ ድሪባ ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለወንድማማችነት መጠናከር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ተመሳሳይ ፌስቲቫሎችን ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ውድድሩ በድምቀት እንዲካሄድ ያስተባበሩ አመራሮች፣ መምህራን እና ባለሙያዎች እንዲሁም ተማሪዎችን በራሳቸውና በጽ/ቤቱ ስም አቶ ከበደ ምሥጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም የክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም አበራ እንደተናገሩት ተመሳሳይ ውድድሮች በመምህራንና በተማሪዎች መካከል ማካሄድ መቀራረብን ስለሚፈጥሩ መጠናከር አለባቸው በማለት ተናግረዋል።
ስፖርት ጤናማ ስለሚያደርግ አጠናክሮ በማስቀጠል የመምህራንን እና የተማሪዎችን ጤና በማጎልበት የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ማድረግና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አሳስበዋል።
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በወረዳ 7 መምህራንና በወረዳ 10 መምህራን መካከል የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ በማድረግ ፌስቲቫሉ በይፋ ተጀምሯል።







