በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የወረዳ አንድ አስተዳደር የሌማት ትሩፋት መርሀ-ግብር በይፋ አስጀመረ፡፡

ህዳር 22/2015 ዓ/ም (አቃቂ ቃሊቲ)

በመርሐ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፣ የክ/ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መዝገበ ይስማው፣ የክ/ከተማው ም/ስራ አስፈጻሚ እና የስራ እድል ፈጠራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር፣ የክብር እንግዶች እና የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኑሮ ውድነት ያለውን ፈተና መቋቋም የሚቻለው የህብረተሰቡን የገቢ አቅም በማጠናከር እንዲሁም የስራ እድል በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም መተግበር ስንችል ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ህብረተሰባችን ውስጥ ትልቅ ድህነት አለ ነገር ግን በየቦታው የሚታዩ ጾማቸውን የሚያድሩ መሬቶች አሉ ይህንን ማስታረቅ እንደሚገባ፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻለው ባለን ነገር ማልማት ስንችል ነውና ማህበረሰቡም ይህንን በመረዳት የዚህ መርሀ-ግብር ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደስታ ፊሊጶስ በበኩላቸው በሌማት ትሩፋት በቂ እና አመርቂ የሆኑ ምርቶችን አቅርበን የተትረፈረፈ ማዕድ በፍቅር የምንቆርስበት፤ በደማችን አጽንተን ያቆየነውን ሉአላዊነታችንን በላባችን ዳግም የምናረጋግጥበትና የምናጸናበት ትልቅ ንቅናቄ ነው በማለት ሁሉም ለዚህ ንቅናቄ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትና ርብርብ እንዲያደርግ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማእከል ለወረዳው በምርምር የበለጸጉ 10 ሺ ዶሮዎችን በዘርፉ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በክቡር ም/ከንቲባው በነፍስ ወከፍ የሚጠቀሟቸው ዶሮዎችን የማረካከብ መርሀ ግብር የተከናውኗል።

በተያያዘም በእለቱ ከሌማት ትሩፋት ጎን ለጎን ከሚከናወኑ የ90 ቀናት እቅድ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካሞችን የቤት እድሳት ለማስጀመር ከበለሀብቶች ጋር ርክክብ ተደርጓል።