የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ አካሄደ።

========================

መጋቢት 11/2015 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ)

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬ ዕለት አካሄዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ድሪባን ጨምሮ ከ12 ወረዳ የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

ለመወያያ መነሻ የሚሆን ሰነድ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በማዘጋጃዊ አገልግሎት አሰጣጥ ቡድን መሪ በሆኑት በወ/ሮ ልደት ታዲዎስ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመብራት ፣ የውኃ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ፣ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን እንዲሁም ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዴት እንፍታ? ከባለድርሻ አካላትስ ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጥያቄዎች በቀረበው የመወያያ ሰነድ ላይ በስፋት ቀርቧል?

በቀረበው የመወያያ ሰነድ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን በተለይም ጽ/ቤቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ከመሰረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ከተጠሪ ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ማካሄዱ መልካም ተሞክሮ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ እንደዚህ አይነት መሰል ውይይቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከመብራት፣ ከውኃ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ ተጠሪ ተቋማትም የተጣለባቸውን አደራ በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ከመድረኩ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየትች የክፍለ ከተማው ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ድሪባ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡ ሲሆን በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደዚህ አይነት መሰል የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንደሚሞጥሉ አያይዘው ተናግረዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ከመብራት፣ ከውኃ፣ ከእሳትና ድንገተኛ እንዲሁም ከቄራ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፈታት ጽ/ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ አንገብጋቢ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት አማራጭ አሰራሮችን ዘርግቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ኃላፊው አያይዘውም ወቅቱ የክረምት መግቢያ ወራት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአስተዳደሩ ለጎርፍ እና ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመው ህብረተሰቡም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሊፈጠሩ ከሚችሉ አደጋዎች ራሱንና አካባቢውን ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።