የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከማኅበረሰቡ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄደ
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት “በደም የከበረ በላብ የታሠረ” በሚል መሪ ቃል በክፍለ-ከተማው ከሚገኙ ከተለያየ ማህበረሰባዊ መሠረት ከተወጣጡ ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበራ ብሩ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መዝገበ ይስማው እንዲሁም ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።
የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መዝገበ ይስማው ሲሆኑ ሰነዱም በሶስት አጀንዳዎች ላይ ማለትም በለውጡ የመጡ ለውጦች፣ የሌማት ቱሩፋቶች እና የሰላም ስምምነቱ አንድምታዎች ዙሪያ የተዘጋጁ ሲሆን በዝርዝር ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
በውይይቱም በመስዋዕትነት የቆመን ሃገር በላብ የሚያፀኑ ዋነኛ ማጠንጠኛ ጉዳዬችን አሳይተዋል በዚህም በማይናወጥ ኢኮኖሚ፣ በአዳጊ ፖለቲካ፣ በሚያስተሳስር ማህበራዊ ገመድ እና ጠንካራ ዲፕሎማሲ ላይ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
መንግስት ባመቻቸው አቅጣጫ አሁን ላይ ወቅታዊ አጀንዳ በሆነው “የሌማት ትሩፋት ” ስራዎችን አጠናክሮ በመስራት የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም እንደ ክፍለ ከተማ 35,403 (ሰላሳ አምስት ሺ አራት መቶ ሶስት) ሰዎችን በማሳተፍ በጦር ሜዳ ደማችንን በኢኮኖሚ ግንባር ላባችንን አፍሰን በርካታ ድሎች ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት በሶስት ዙሮች ከፍተኛ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ተስተናግደዋል፤ አሜሪካ በህወሃት ፈረስ ላይ መጋለቡን ለማስቆም የአፍሪካዊያን ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱም ተጠቅሷል።
መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው በህዝባችን ደጀንነት፣ በመከላከያችን ጀግንነት እና በመንግስታችን ብስለት አሁን ላይ የትግራይ እናቶች እና ጦርነቱ ሲካሄድባቸው የነበሩ አካባቢዎች የሰላም አየር እየተነፈሱ ነው ብለዋል።
በተያያዘም አሁን ላይ በትኩረት በተያዘው የሌማት ቱርፋት ዘመቻ ላይ አመራሩ እና ህዝቡ በቁርጠኝነት በመስራት በጦርነቱ የታየውን አሸናፊነት በምግብ ራሳችንን በመቻል ለልመና የሚዘረጉ እጆች ለስራ እንዲነሱ በማድረግ በእያንዳንዱ ቤት የሚጎረስ ዳቦ ማስገኝት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበራ ብሩ በበኩላቸው እኛ ኢትዮጵያዊያን የዕምቅ ሀብት ባለቤት ሆነን በድህነት መታወቅ የለብንም በዕለተ ተዕለት የምንመገበው ምግብ ላይ አስፈላጊ እና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን በማምረት እንደ ብርቅ የንቅጦት ተደርገው የሚቆጠሩ ምግቦችን ማግኝት እንችላለን ብለዋል።
ተወያዮችም የቀረበው ሰነድ ይበል የሚያስብል መሆኑን በመግለጽ ፣የተጀመረውን ሰላም በማስጠበቅ የሌማት ትሩፋቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከአመራሩ ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፤ በተጨማሪም አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እና ሀሳብ አስተያየቶችን አንስተዋል።
በመጨረሻም ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረክ መሪዎቹ ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸው መድረኩ ድምዳሜ አግኝቷል።