የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አስተዳደር በ2ኛ ዙር የ90 ቀናት ሰው ተኮር ዕቅድ ዙሪያ ከክ/ከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ።
========================
መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ)
ውይይቱ የክ/ከተማ እና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት የተደረገ ሲሆን በአሰተዳደሩ በ2015 ዓ.ም የመጀመርያ ዙር የ90ቀናት ሰው ተኮር እቅድ ላይ በሌማት ትሩፋት ማጠናከር ፤ ምቹ የስራ አከባቢ በመፍጠር፤ አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል፤ በስራ ዕድል ፈጠራ፤ በማስ ሰፖርት፤ ገበያ በማረጋጋት፤ በአካባቢ ጽዳትና ውበት፤ በሰላምና ጸጥታ የተከናወኑ ተግባራትና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ከሳምንት በፊት መመረቃቸው የሚታወስ ነው።
ተግባሩ ከመጀመሩ በፊት ከአስፈጻሚ አካላትና ከበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቂ ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደ ስራ በመግባት በወረዳ ተቋማትና በክ/ከተማ አስተዳደሩ አመርቂ ውጤት እንደተመዘገበ በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ተጠቅሷል።
25 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ ለአቅመ ደካማ እና ለአረጋውያን ማዕድ የማጋራት ተግባር መፈጸሙ የተጠቀሰ ሲሆን በተግባራቱ ባለሀብቶች መሳተፋቸው እና ውጤት ማስገኘቱም ተመላክቷል።
ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ባለሀብቱ ወደ ስራ ከገባ በኃላ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ፕሮጀክትን ማጓተት፤ የግንባታ ግብዓት እጥረት፤ ወጥ በሆነ መልኩ ክትትልና ድጋፍ አለማድረግ እና መሰል ተግዳሮቶች ተስተውለዋል።
ዝቅተኛ አፈጻጸም ከተመዘገበባቸው ተግባራት መካከል የቤት እድሳት ሲሆን 120 ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ 78 ተጀምሮ 45ቱን ማጠናቀቅ እንደተቻለና ቀሪዎች በጅምር ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በሁለተኛው ዙር የዘጠና ቀናት እቅድ ከ18 ሺ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን ያልተጠናቀቁትን ጨምሮ አዳዲስ ተግባራትንም በ12ቱ ግቦች ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።
ተሳታፊዎቹ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በስራ እድል ፈጠራ ጥራት ላይ ሊተኮር እንደሚገባ እና የሥራ ዕድሉ የተፈጠረለት በራሱ ሊመሰክር ይገባል፤ የቤት እድሳት አፈጻጸም መሻሻል አለበት፤ የተጀመረው ባለአራት ወለል ህንጻ ግንባታ ሊፋጠን ይገባል የሚሉ እና በሌሎች ተግባርት ዙሪያ አስተያየት ሰጥተዋል።
መድረኩን የመሩት የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አበራ ብሩ እንደተናገሩት የዘጠና ቀናት እቅድ ከመደበኛው እቅድ ጋር በማስተሳሰር ሊሰራ ይገባል ሲሉ አዳዲስ ተግባራትን በማቀድ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለተግባራቱ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ የክትትልና ድጋፉ ተግባር ወሳኝ መሆኑን ከመጀመሪያው ዙር ልምድ በመውሰድ በቀጣይም የተጠናከረ ክትትል ለማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተገልጿል ።