የክ/ከተማው ንግድ ጽ/ቤት የዋጋ ንረት በመከላከልና ገበያ በማረጋጋት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

=======================

መጋቢት 7/2015 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ)

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽ/ቤት በገበያ ማረጋጋት ዙሪያ ከእህል ነጋዴዎች፤ ከወፍጮ ቤት ባለቤቶች፤ ከሸማች መብት ጥበቃ ተወካዮች፤ ከነጋዴ ማህበራት፤ ከወረዳ ህብረት ስራ ማህበራት እና ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል።

በውይይቱ በተለይ ከሰብል ምርት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረትን ለማርገብና የገበያ መረጋጋት እንዲፈጠር ነጻ ገበያ መጠናከር አለበት፤ አቅርቦቱ ከክልሎች መጠናከር ይኖርበታል በማለት ተሳታፊዎች ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት ከነዋሪው ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን አቅርቦት ሊኖር ይገባል፤ ቁጥጥርና ክትትሉን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ደላላን መከላከል እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።

በተነሱ ሀሳቦች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ደምሴ የዋጋ ንረትን ለማርገብና የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን አለበት ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱ እና የዋጋ ንረቱ ዓለም አቀፍ ችግር ቢሆንም እንደ ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከፍተኛ በጀት በመመደብ በሪቮልቪንግ ፈንድ በዩኒየን በኩል የሸማቹን አቅም በሚመጥን መልኩ ምርት እየቀረበ እንደነበረ እና አሁንም እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

የህብረት ስራ ማኅበራት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ የሱፍ ይመር በበኩላቸው የሚቀርበውን ምርት ለተጠቃሚው ፍትሀዊ በሆነ መልኩ እንዴት መቅረብ እንዳለበት ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በቂ ምርት እየቀረበ በመሆኑ ምርቱን በመቀበል ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የመሰረታዊ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የተመሰረቱለትን ዓላማ ግብ ሊያሳኩ ይገባል በማለት አቶ የሱፍ ተናግረዋል።