የተዋበች ክ/ከተማ ካልፈጠርን የተዋበች አዲስ አበባን መፍጠር አንችልም!” – አቶ አለማየሁ ሚጀና

“ዛሬ ለተሰጠኝ አደራ እኔም በታማኝነት፣ በቅንነት ባለዉ ሕግና አሠራር በገባሁት ቃል መሠረት ቃሌን ጠብቄ የሕዝቡን አደራ በማክበር ሥራዬን ለመፈፀም ዳግም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡
አደራዉን ስቀበል ትልቅ ኃላፊነት ስለሆነ ሐሳብ ያለበት ነዉ፤ የሚያስተኛ አይደለም፡፡ ቃላችንን ለመፈፀም የምንችለዉ እንደ እግር ኳስ ቡድን በጋራ ኳሱን በደንብ መጫወት ስንችል ብቻ ነዉ ጎል ማስቆጠር የሚቻለዉ፡፡ ድህነትን ማሸነፍ ግዴታ ነዉ፡፡ አሁን ላይ የጠላነዉ ቁጥር አንድ ጉዳይ ቢኖር ድህነት ነዉ፡፡ ከድህነት ጋር ደግሞ አብረን መኖር አንችልም ብለን ቃል ገብተናል እንደፓርቲያችንም ሕዝቡም የመረረዉ ነገር ቢኖር ድህነት ነዉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ትልቅ ንቅናቄ መሥራት ያስፈልገናል፡፡
እንደ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ደግሞ በርካታ የሕዝብ አጀንዳዎች እንዳሉ እኔም በደንብ አዉቃለሁ፡፡ በዚህ ሁለት አመት ተኩል ጊዜ ክ/ከተማዉን ደጋግሜ ጎብኝቻለሁ፤ የሱፐርቪዥን ስራዎችን ሠርቻለሁ፡፡ ያሉ የሕዝብ ጥያቄዎችን በዚሁ አጋጣሚ ለማወቅ እድል ሰጥቶኛል፡፡
በርካታ የመሠረተ-ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ነበሩ፤ በዚሁ ልክ ደግሞ መንግስት ባለዉ አቅም ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ምላሽ የሰጣቸዉ ፈርጀ ብዙ ናቸዉ፡፡ የሕዝብ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ የመጣበት፤ ያለዉ አመራር ሌት ተቀን ለፍቶ ያመጣቸዉን ዉጤት በማስጠበቅ ያሉ ክፍተቶችን ደግሞ በማረም አብረን ተረባርበን ለዉጤት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ለወጣቱ እና ለነዋሪዉ የሥራ እድል መፍጠር ላይ መረባረብም ይጠበቃል፡፡
የኑሮ ዉድነት ችግር የክ/ከተማችንም ፈተና ነዉና በዚህ ላይም በመሥራት ዉጤት ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ ከተማችንን ወደ ስታንዳርድ ለማምጣት፤ የተዋበች ክ/ከተማ ካልፈጠርን የተዋበች አዲስ አበባን መፍጠር አንችልም፡፡ ንፁህ የሆነች ክ/ከተማ፣ ንፁህ የሆነ መንደር፣ ንፁህ የሆነ ብሎክ መፍጠር ካልተቻለ የምንፈልጋት አዲስ አበባን መፍጠር አንችልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ወረዳ እስከ ብሎክ ድረስ ያለዉ አደረጃጀት የአረንጓዴ ልማት፣ ጽዳትና ዉበት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና ከአለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማት ከተማ ናት፤ ስለዚህ ይህቺን ፈርጣማ ከተማ ደረጃዋን በማስጠበቅ ስሟን ማስጠበቅ ያስፈልጋልና በዚያዉ ልክ እንሠራለን ማለት ነዉ፡፡ ለዚህም የሕዝቡ እና የአመራሩ ቅንጅት ያስፈልጋል፡፡
በከተማ ግብርና፣ በጤና፣ በትምሕር፣ በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎቹም ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት እንሠራለን፤ የሌማት ትሩፋትም ብዙ ፕሮግራሞች ተቀርፀዋል፡፡ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ላይ እንደ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ብዙ እቅዶች ታቅደዋል፡፡ ሁሉም እቅዶች የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ናቸዉና የህዝቡ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስሉ እናዉቃቸዋለን ቆጥረን ለሕዝቡ ምላሽ መስጠት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ስኬት በተለይ የምክር ቤት አባላት ከጎናችን መቆም አለባቸዉ፡፡ ስናጠፋም ልንመከር ይገባናል፤ ስናለማ ምሥጋናዉ የጋራችን፤ ዉጤቱም ተጠቃሚነቱም የሕዝብ ነዉ የሚሆነዉ፡፡
የተሻለች ክ/ከተማ ለማድረግ ያለንን አቅም በሙሉ አሟጠን እንጠቀማለን፤ እንሠራለን፤ ቃላችሁን እንጠብቃለን!
የስኬት፣ የልማትና የብልፅግና ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡”

አቶ አለማየሁ ሚጀና
የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ
መጋቢት 08 ቀን 2016 ዓ.ም